Report

ትግራይ ላይ የሚካሄደው ጦርነት በሌላ ኢትዮጵያዊት ዓይን (ክፍል 1)

ስለዚህ ጦርነት ሳስብ በነገሮች አለመጎዳቴን ሳውቅ ህይወት ሁለተኛ እድል እንደሰጠችኝ ፈጣሪም የቤተሰቤን እንባ እና ፀሎት እንደተቀበለ አምናለሁ።

Published

on


የፀሐፊዋ መገቢያ (ስሟ ሊገለፅ ኣልፈለገችም)፦ ትግራይ ውስጥ ለ1 አመት ከ8ወር ኖሬአለሁ። ጦርነቱ ከመታወጁ በፊት ህይወት መልካም ነበር። ማንም ሰው ይሄ እንዲገጥመው አልመኝም። ጦርነቱ ከተጀመረ ለ20 ቀናት የገፈቱ ቀማሽ የችግሩም ተቋዳሽ ነበርኩ።


ስለዚህ ጦርነት ሳስብ በነገሮች አለመጎዳቴን ሳውቅ ህይወት ሁለተኛ እድል እንደሰጠችኝ ፈጣሪም የቤተሰቤን እንባ እና ፀሎት እንደተቀበለ አምናለሁ። ትግራይ ክልል ከባለቤቴ ጋር መኖር ከጀመርን አመት እና የተወሰኑ ወራቶች አስቆጥረናል።

ሁለታችንም የመንግስት ሰራተኞች ነን። በጥቅምት 24 የተፈጠረው ነገር ሲሆን የ7 ወር እርጉዝ ነበርኩ። ወደ እናቴ ጋር ለመሄድ ትኬት ቆርጬ ነበር። ሌሊት 7 ሰአት አካባቢ ነበር ኔትወርክ የጠፋው፤ ይመጣል የሚል እንጂ ይሄ ነገር ስለመፈጠሩ ምንም ፍንጭ የለንም ነበር። እጃችን ላይ የነበረን ገንዘብ 200 ብር ነበር። ጠዋት ላይ የትግራይ ክልልን መግለጫ ሰማን። ስሰማ በጣም አለቀስኩ ። አስቤዛ ለማድረግ በቂ ገንዘብ የለንም። በዛ ላይ እኔ ከሄድኩ ከአንድ ወር በሁዋላ ባለቤቴ እንዲመጣ ስለተነጋገርን እህል አልሸመትንም ነበር። ጓደኞቼ ደግሞ እጃቸው ላይ 30 ብር ብቻ ነበር የነበራቸው። እነሱም ከሰው ተበድረው አስቤዛ አደረጉ። ከዛ በሁዋላ ወጪው እንዳይበዛብን አንድ ላይ መብላት ጀመርን። መብራት ስለሌለ እንጀራ መግዛት ጀመርን (አንድ እንጀራ 15 ብር)…ሳንጠግብ መብላትን ተለማመድን። የእኛ ዘይት አልቆ የእነሱ ትንሽ ስለነበር የእነሱን መጠቀም ጀመርን። ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰውነቴ ሲጎዳ የጓጓሁለት ፅንስም አለማደጉን ማስተዋል ባልፈልግም ባለቤቴ እና ጓደኞቼ ግን እያስተዋሉት ነበር። ከሁሉም በላይ ጭንቀቱ ሁላችንንም ቅስም እየሰበረን ነበር።

በመጨረሻ ከውስጥ ገቢ ተብሎ ደሞዝ ተሰጠነ። በዛውም ከእዚህ በሁዋላ መቼ እንደሚሰጣችሁ ስለማይታወቅ ቆጥባችሁ ተጠቀሙ የሚል መልእክት አስተላለፉልን። ይህ በሆነ በ4ኛው ቀን ቁርስ ሰርተን ልንበላ ባለቤቴ ዳቦ ሊገዛ ወጥቶ መጥፎ ዜና ይዞልን መጣ። በእኛ አቅራቢያ ያለች ከተማ ጋር የከባድ መሳሪያ ድምፅ መኖሩን እና ይሄ ምንሰማው ድምፅ የእሱ መሆኑን ነገረን። ተመላላሽ ሰራተኛችንም መጥታ ተመሳሳይ ነገር ነገረችን። ሰዉ እየሸሸ መሆኑን እና እኛም እንድንሄድ። የእኔ ቤተሰቦች ትግራይ ክልል የሉም።

የእሱ ቤተሰብ ጋር ለመሄድ ትራንስፖርት የለም። የመጀመሪያ እርግዝናዬ ነው። ረሀብ እና ጭንቀት ከእኛ አልራቁም። ከሰአታት በሁዋላ መንገድ በተኩስ ምክንያት ሊዘጋ እንደሚችል ባለቤቴ ሰማ። ከዛ የመቀሌ መኪና ማፈላለግ ጀመረ። በድብቅ የሚሄዱ ማለት ነው። እንደምንም መቀሌ ደረስን። ሰሜናዊት ኮከብ መቀሌ የወትሮው ውበቷ ርቋታል። ከተማው ፀጥ ረጭ ብሏል። የባለቤቴ ጓደኛ ጋር ደውለን እሱ ጋር አረፍን። መቀሌ በገባን በሁለተኛው ቀን ከባለቤቴ ጋር ሮማናት ሚባል አካባቢ እያለን የሆነ ድንገተኛ አስፈሪ ድምፅ ሰማን። እየሮጥን ልብስ ስፌት ቤት ገባን እና ተደበቅን።

መቀሌ በአየር እየተደበደበች ነበር። የነበረው የሰዉ ጩኸት እና ትርምስ አሁንም ፊቴ ላይ አለ። በሁዋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ ቦምብ እንደተጣለ ሰማን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Exit mobile version